- We Strive to Empower Poor Women and Girls
“ ጠንክረን ከሠራን ነገም ሌላ ቀን ነው”
የተወለድኩት ጎንደር አውራጃ ልዩ ስሙ አርማጭሆ ተክል ድንጋይ ይባላል፡፡ በ1958 ዓ.ም ከእናቴ ወ/ሮ ፀጋነሽ ጀንበሬ እና ከአባቴ አቶ ዳኞቸው ወንዳፍራው ተወለድኩኝ፡፡ የአንድ ዓመት ልጅ እያለሁ እናትና አባቴ በመለያየታቸው ምክንያት አባቴ ሌላ ሚስት አገባ፡፡ እኔም ለጥቂት ጊዜ ከእናቴ ጋር ከኖርኩኝ በኋላ ለአባቴ የነበረኝ ፍቅር ከባድ ስለነበረ ከአባቴና ከእንጀራ እናቴ ጋር መኖር ጀመርኩ፡፡ያ ኑሮ ግን የስቃይ ኑሮ ነበር ፡፡
እድሜዬ ለትምህርት ሲደርስ ትምህርቴን ለመማር ስል እናቴ ጋር መኖር ጀመርኩኝ፡፡ መደበኛ ትምህርቴንም እዚያው ትክል ድንጋይ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ ተማርኩ ፡፡ ነገር ግን ሴት ተማሪ ከትምህርት ቤት አርግዛ ብትመጣስ እየተባልኩኝ ተፅእኖ እና ቡዙ ችግር ከቤተሰቦቼ ደረሰብኝ፡፡ በስተመጨረሻም ማግባት አለባት የሚል ውሳኔ ተወሰነብኝ፡፡ እኔም ምንም አማራጭ ስላልነበረኝ በ1969 ዓ.ም ነሐሴ ወር ላይ አገባሁኝ፡፡ ከዚያም ከባለቤቴ ቤተሰቦች ጋር እየኖርኩኝ የመጀመሪያ ልጃችንን ወንድ ልጅ ወለድኩኝ፡፡
በደርግ ጊዜ ባለቤቴ በፖለቲካ ምክንያት ታሰረ እኛም ከባድ ችግር ውስጥ መኖር ጀመርን፡፡ አንድ ዓመት ከሶስት ወር በኋላ ተፈቶ ቢመጣም ያው ችግር ግን አልተፋታም ነበር፡፡ እኔም ሁለተኛ ልጄን ወለድኩኝ ያን ጊዜ ያሳለፍኩትን ችግር ግን እስከዛሬ ድረስ አልረሳውም፡፡ ችግሩም ሲብስብኝ የአንድ ዓመት ልጄን ጥዬ ወደ አስመራ በመጥፋት የሰው ቤት በወር 30 ብር ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩኝ፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል ከሠራሁኝ በኋላ የሰው ቤት ሥራ ሲመረኝ መንግስት ቤት ተቀጠርኩኝ እዚያም እየሠራሁኝ ወታደር አገባሁኝ፡፡
በጉጉት የቀረውን ትምህርቴንም እንደገና እስከ 12ተኛ ክፍል ድረስ አስመራ ተማርኩኝ፡፡ከባለቤቴ ጋርም አንድ ልጅ ለማፍራት ችያለሁኝ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ግን በ1983 ዓ.ም ከአስመራ ተፈናቅለን አዲስ አበባ ገባን፡፡ አባቴ ጋር መኖር ጀመርኩኝ እሱም የቀበሌ ቤት ስለነበረው ለ 8 አመታት አባቴ ላይ ጥገኛ ሆኜ ሎውዝ እና ሲጋራ እየሸጥኩኝ ልጄን ቄስ ትምህርት ቤት እያስተማርኩኝ ያገኘነውን እየበላን መኖር ጀመርን፡፡
በ1998 ዓ.ም አንዲት ገደኛዬ ስለራሴድ ነገረችኝ እኔም እያቅማማሁኝ በስብሰባው ላይ ተገኝቼ ስለድርጅቱ ሰማሁኝ ይህም ቢሆን ግን አላመንኩበትም ነበር እንዲያውም ቁጠባ ብለው ገንዘቤን ሊወስዱብኝ ነው በማለት አቅማምቼ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን የሴቶችን ህይወት የሚቀይር ድርጅት መሆኑን አወኩኝ ቁጠባም ጀመርኩኝ፡፡ ቁጠባዬንም እየቆጠብኩኝ ለስልጠና ተጠራሁኝ ከስልጠናው ስለ ገንዘብ አያያዝ፣ ስለጤና፣ ቤተሰብ አያያዝ፣ በጊዜ አጠቃቀም በአጠቃለይ በህይወቴ ላይ ትልቅ ለወጥ እንዳመጣ ጠቅሞኛል፡፡
የመጀመሪያ ዙር ብድር 500 ብር በመበደር ከረሜላ ፣ ማስቲካ ፣ ብስኩቶች፣ በተለያዩ ቦታዎች እያዞርኩ መሸጥ ጀመርኩ ብድሬንም በ6ወር ውስጥ ከፍዬ ጨረስኩ፡፡ የሁለተኛ ዙር ብድሬንም በመውሰድ ንግዴን ማስፋፋት ተያያዝኩት ብድሮቼን እየከፈልኩኝና ተጨማሪ ዙር ብድሮችን እየወሰድኩ ንግዴን በተሻለ ሁኔታ በማስፋፋትና ከረሜላ ፣ ማስቲካ ፣ ብስኩቶች፣ ካላሲዎች፣የሳንቴም ዝርዝሮችን እና ተያያዚነት ያለቸውን ነገሮች ከለሊቱ10:30 እስከ 2:00 ሰዓት እና ከምሽቱ 12:00 እስከ 4:00 ሰዓት በተለያዩ ቦታዎች እያዞርኩኝ መሸጤን ተያያዝኩት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥነት ያላቸውን ሥራዎችንም እሰራለሁ፡፡ በዚህ ወቅት ንግዴ ብቻ ሳይሆን በቤት ውስጥ ኑሮዬና እድገቴ ጨመረ ቤቴንም ያደስኩ ሲሆን በቤቴ ውስጥ የለስላሳና የአምባ ዉሃ መጠጦችን እሸጣለሁ፡፡ በተጨማሪም የእቁብ ሰብሳቢ በመሆን ኮሚሽን ይከፈለኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የ20000 ብር ተበዳሪ ነኝ፡፡ማሲቲካ በመነገድ የጀመርኩት ሥራ አሁን የምሸጠውን የእቃ አይነት በመጨመር ንግዴን እስፋፍቻለሁ ፡፡ በህይወቴ ላይም መግለፅ የማልችለው ለውጥ ነው ያገኘሁት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከላይ የገለፅኩላቹሁን ሥራ እየሠራኩኝ ከአዲስ እንተርናሽንናል ባንክ 10 እጣ አክሲዮን ገዝቻለሁ እንዲሁም ከሀበሻ ቢራ 7ዕጣ ገዝቻለሁ፡፡ 15000 ብር ቁጠባም በማህበሬ ውስጥ አለኝ፡፡ ልጆቼንም ቢሆን ከራሴድ ባገኘሁት ብድር እየሠራሁኝ ነው ያስተማርኩት በአሁኑ ሰዓት አንደኛዋ ልጄ በአየር መንገድ ተቀጥራ ትሰራለች ሌላኛው ደግሞ በ 5ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው፡፡
ለሴት እህቶቼ የምመክረው ተስፋ ሳንቆርጥ ጤናን በመጠበቅና ከእንቅልፍ ሰዓታችን በመቀነስ ለሥራ በማዋል ነገም ሌላ ቀን ነው ብለን ጠንክረን ከሠራን ሁላችንም መለወጥ እንችላለን ፡፡
ራሴድን ምን ብዬ እንደማመሰግነው አላውቅም ምክንያቱም ህይወቴ መስመሩን እንዲይዝ ረድቶኛል፡፡ ከዚህ በፊት ብር የማገኝበት አጋጣሚ ቢኖርም እንኳን የአያያዝ ችግር ነበረብኝ አሁን ግን ያገኘሁት ስልጠና ተግባራዊ በማድረግ ለዚህ በቅቻለሁ፡፡ ለደሀዋ ሴትና በዋስ መበደር ለማይችሉትም ያለዋስ በማበደር ለስኬት ማብቃቱ ታላቅ ነገር ነው፡፡
ሰርካለም ዳኛቸው ወንዳፍራው ነኝ ከበርቺ ማህበር ቀበሌ 10/11/11
