• We Strive to Empower Poor Women and Girls

“በልጅነቴ ባገኘሁት ኖሮ”

እለቱ ጥር 27 ቀን 2003 ዓ.ም. ጉዞ ወደ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 07/08 ወደ ወይዘሮ ሮማን አያሌው ቤት ጎራ አልኩ፡፡ ከዚያም የተለመደው የእግዚአብሔር ሰላምታዬን አቀረብኩ፡፡ እሳቸውም ከሚሰሩበት ጓዳ ብቅ በማለት ግቢ እግዚአቢሔር ይመስገን ብለው ለሰላምታዬ ምላሽ ሰጡኝ፡፡ እኔም የመጣሁበትን አላማ በመግለፅ ታሪካቸውን እንዲያወጉኝ ጠየኳቸው፡፡ ከዚያም የሚከተለውን አወጉኝ፡፡
ሮማን አያሌው እባላለሁ ከእናቴ ከወ/ሮ አጥናፏ በለይ እና ከአባቴ ከአቶ አያሌው ገ/ማሪያም በ1937ዓ.ም በአሩሲ ከተማ ልዩ ስሙ ሁሩታ በተባለ ትንሽ መንደር ተወለዱኩ፡፡
እድሜዬ ለትምህርት ቢደርስምና የትምህርት ፍላጎት ቢኖረኝም በአገሩ ላይ ምንም አይነት የትምህርት እድል አልነበረም፡፡ እኔም 12 ዓመት እስኪሞላኝ ድረስ በግብርና የሚተዳደሩ ቤተሰቦቼን ሳገለግል ከቆየሁ በኋላ በአገሩ ባህል መሰረት አኔም እንደእድሜ እኩዮቼ በለጋ እድሜዬ ተዳርኩ፡፡ ልጆችም አፍርተን መኖር ጀመርን፡፡ ከ37 ዓመት የትዳር ቆይታ በኋላ ባለቤቴ በህመም ምክንያት ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡
ባለቤቴ ከሞተ ከጥቂት አመታት በኋላ ልጆቼ አዲስ አበባ ወደ ላፍቶ አካባቢ ስለሚኖሩ እነሱ ጋ መጣሁ፡፡ ልጆቼ ጋር ለተወሰነ ዓመት ከኖርኩ በኋላ ለምን እራሴን ችዬ አልኖርም በማለት ወደ አቃቂ አካባቢ ቤት ተከራይቼ ኑሮን አሐዱ ብዬ ጀመርኩ፡፡
እዚያው የተከራየሁበት ቤት ውስጥ እንጀራ፣ ዳቦ፣ ብስኩትና አትክልቶችን በመሸጥ መተዳደር ጀመርኩ፡፡ ንግዱንም ስጀምረው በ500 ብር ካፒታል ነበር፡፡ እንዲህ እየሠራሁ እያለ ሥራዬን ያየች እዚያው አካባቢ የምትኖር አንዲት ጎረቤቴ “ለምን ራሴድ አትገቢም የገንዘብ ችግርሽም ሆነ ሌሎች ችግሮችሽን ይቀረፋሉ” ብላ ስትለኝ መጀመሪያ አቅማማሁ፡፡ ነገር ግን ለምን አልሞክረውም በማለት በ1998 ዓ.ም ራሴድ አባል ሆኖ ተመዘገብኩ፡፡ ቁጠባዬን እየቆጠብኩ ለመሰረታዊ የንግድ ክህሎት ስልጠና ተጠራሁ፡፡ ሥልጠናው ቁጠባን፣ የጊዜ አጠቃቀምን፣ ሥራን ባለመናቅ እንዴት ማደግ እንደሚቻል የሚያስተምር በመሆኑ በአጠቃላይ ለአሁኑ እድገቴ ትልቁ መሰረት ሥልጠናው ነው፡፡ ይህን ሥልጠና በልጅነት እድሜዬ ባገኘው ኖሮ ዛሬ ላይ እኔም ባለሃብት እሆን ነበር፡፡
ከዚያም የመጀመሪያ ዙር 500 ብር በመበደር ንግዴ የነበረበትን ሁኔታ አሻሻልኩ፡፡ ምግብም ጨምሬ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ከሥልጠናዎቹ ያገኘሁትን እውቀት እየተገበርኩ ብድሬን በመመለስ የ2ተኛ እና የ3ተኛ ዙር ብድሮችንም በመውሰድ የተለያዩ ለሥራዬ የሚሆኑ ፍሪጅ፣ የችብስ መጥበሻ ማሽን፣ የቡናና የሻይ ማሽን፣ የለስላሳ ሳጥኖች፣ የውሃ ማጠራቀሚያ(ሮቶ) እንዲሁም የምሠራበትን ቤት ውስጡን በማደስ በአሁኑ ሰዓት የ11600/እስራ አንድ ሺህ ሥድስት መቶ/ ብር ተበዳሪ ሆኛለሁ፡፡ በማበህሬ ውስጥ ያለኝ ቁጠባ 7000 /ሠባት ሺህ / ብር በላይ የደረሰ ሲሆን በሳምንት ውስጥም 300 ብር የብድር ተመላሽ አደርጋለሁ፡፡ የንግዴም ካፒታል 50.000 ብር/ሃምሳ ሺህ/ ብር ደርሷል፡፡ በዚህ ሥራዬ 350 ብር የመኖሪያ ቤት ኪራይ እየከፈልኩ ስድስት ቤተሰቦቼን የማስተዳድረው እኔ ነኝ፡፡
በራሴድ በዚህ አመት ታህሳስ ወር በተዘጋጀው የካፒታል ውድድር ሶስተኛ ወጥቼ ዘመናዊ የጁስ መጭመቂያ ማሽን ተሸላሚ ሆኛለሁ፡፡ ወደፊት ይህንኑ ሥራየን አስፋፍቼ ለመቀጠል ሃሳብ አለኝ ፡፡ ማንኛውም ሰው ሥራን ካልናቀ ትልቅ ቦታ መድረስ ይቻላል እያልኩ የምሰናበታችሁ ሮማን አያሌው ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 07/08/09 ከቢያምር ማህበር

Who's online

There are currently 0 users and 2 guests online.